buy cialis online buy viagra online vicodin online የሥራ አስኪያጅ መልዕክት

የሥራ አስኪያጅ መልዕክት

ከሁሉ አስቀድሜ ለተከበራችሁ የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር አባላትና የመንደቅ መጽሄት አንባብያን በሙሉ ሰላምታዬን አቀርባለሁ፡፡  እንደሚታወቀው ማህበሩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ከሚንቀሳቀስባቸው ተግባራት መካከል አንዱ አባላቱ በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ አገራት ተዘዋውረው አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን  በማግኘትና ልምድ በመቅሰም ግንዛቤያቸውን ማሳደግ የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት መሆኑ ይታወቃል፡፡ማህበሩ  በውጭ አገር በሚካሄዱ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽኖችና ኮንፍረንሶች ላይ አባላቱ እንዲሳተፉ  እያደረገ ያለው ድጋፍ ከዚህ አኳያ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ ሆኖም ግን በአገር ውስጥ የሚካሄዱ ትልልቅ የግንባታ ስራዎችን/ፕሮጄክቶችን በማስጎብኘት አባላት ጠቃሚ ትምህርት የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት የሚጠበቅብን ቢሆንም አስከቅርብ ጊዜ ድረስ ትኩረት ተሰጥቶት ሳይሰራበት ቆይቷል፡፡ ይህን በተመለከተ በቅርቡ የተጀመረውና እየተደረገ ያለው ጥረት የሚያበረታታ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ማህበሩ አባላቱን በማስተባበር ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጄክትን እንዲጎበኙ ያደረገ ሲሆን ከስልሳ በላይ የማህበሩ አባላት «ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የሀገራችን የኮንስትራክሽን እድገት ነጸብራቅ ነው» የሚል መርህ አንግበው መጋቢት 8 ቀን 2006 ዓ.ም በቦታው ተገኝተው በመጎብኘታቸው የተሰማቸውን ትልቅ ደስታ ከማየታችንም በላይ  ለፕሮጄክቱ መሳካት አቅማቸው የፈቀደውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ በድጋሚ ቃል የገቡበትን አጋጣሚና የፈጠረባቸውን ከፍተኛ የሆነ ተነሳሽነት ለመመልከት ችለናል፡፡ በቀጣይም ሌሎች ተመሳሳይ የጉብኝት ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት የአባላቱን ፍላጎት ለማርካት ማህበሩ አቅሙ በፈቀደ መጠን ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራበት እንደሚገባም ተገንዝበናል፡፡

 

የዚህ አይነት ዝግጅቶች መካሄዳቸው በአንድ በኩል ግንዛቤን ስለሚያሳድጉ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር ስለሚያግዙ ተቋራጩ ወደ ከፍተኛ ደረጃ በመሸጋገር በአገር ውስጥ ብሎም በጎረቤት አገሮች በሚካሄዱ ትላልቅ የግንባታ ሥራዎች ላይ መሳተፍ የሚያስችለውን ራዕይ በመሰነቅ ለለውጥ እንዲነሳሳ የሚረዳውን የሥነ-ልቦና ዝግጁነት የሚፈጥሩለት መልካም አጋጣሚዎች  ሲሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ በአባላት መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ በማጎልበት ለጋራ ጥቅም ተቀራርበውና ተባብረው በሚሰሩበት መንገድ ላይ በመምከር ራሳቸውን ብሎም የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝም እምነታችን ነው፡፡
በመሆኑም የተጀመሩት እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በዚህ አጋጣሚ እያረጋገጥን ማህበሩ እያደረገ ያለውን ጥረት በመደገፍ ለስኬታማነቱ ዘወትር ከጎናችን ለቆማችሁት አባላትና ባለድርሻ አካላት በሙሉ ያለንን አክብሮት በማህበሩ ጽ/ቤት ሠራተኞችና በራሴ ስም ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡