buy cialis online buy viagra online vicodin online የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ኘሮጀክትን እኔ እንዳየሁት

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ኘሮጀክትን እኔ እንዳየሁት

በኢንጅነር አብርሃም ደምሴ


ከጥቂት ቀናት በፊት መጋቢት 8/2006 ዓ.ም ቁጥራቸው 60 ከሚሆኑ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር አባላት ጋር በመሆን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ኘሮጀክት ለመጐብኘት ዕድል አግኝቼ ነበር፡፡

ባለፉት 30 ዓመታት በሀገሪቱ ውስጥ በተከናወኑ የተለያዩ አነስተኛና ከፍተኛ የኮንስትራክሽን ኘሮጀክቶች ላይ የመስራትና በቅርበት የማየት ዕድል አጋጥሞኛል፡፡ ነገር ግን እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኘሮጀክት ሀገራዊ ፋይዳው የበዛ ዜጐችን ከዳር እስከዳር ያንቀሳቀሰና ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል አንድ አድርጐ ትልቅ ተነሳሽነትን የፈጠረ ኘሮጀክት አይቼ አላውቅም፡፡ ለዚህም ነው የዚህን ኘሮጀክት ጉብኝት በትልቅ ጉጉትና ተስፋ እንድንጠብቀው ያደረገኝ፡፡ ጉብኝቱም እጅግ የተሳካና የሀገሪቱም የወደፊቱ ዕጣ ፈንታ ብሩህ ሊሆን እንደሚችል ያመላከተ መሆኑን ያረጋገጠልኝ ነው፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት በድርቅና በምግብ እጥረት በተደጋጋሚ መጠቃቷ በዓለም ላይ በድህነት የምንታወቅበት ልዩ መለያችን እስከ መሆን ደረጃ የደረሰበት ሁኔታ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በአሁኑ ሰዓት እየተለወጠ ከመምጣት አልፎ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ልታደርገው ብቻ ሳይሆን ልትሞክረው አትችልም ይባል የነበረውን ሰፋፊ የልማት ኘሮጀክቶችን በራሷ አቅም በማከናወን ላይ ትገኛለች፡፡ከነዚህ ኘሮጀክቶች አንዱና ትልቁ በአባይ ወንዝ ላይ መገንባት የጀመረው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ኘሮጀክት ነው፡፡
የአባይን ወንዝ እስከዛሬ የነበረውን ሁኔታ ስናይ የኢትዮጵያን ለም አፈር ሸርሽሮ ከመውሰድ አልፎ በታችኛው ተፋሰስ አገራት በተለይም ግብፅ በጠላትነት እንድትታይ በማድረግ የግጭትና የጦርነት መንስኤ እንደነበር  ያለፈው ታሪካችን ያሳያል፡፡ በጣም ወደ ኋላ የነበረውና ታሪክ እንኳን ትተን በ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ያለውን ስናይ ግብፆች የአባይን መነሻ ለመያዝ በነበራቸው ፍላጐት የተነሳ በርካታ ሠራዊት አሰልፈው በህዳር 1867 ዓ.ም ጉንዳጉንዲ ላይ እና በመጋቢት 1868 ዓ.ም ጉራዕ ላይ ከአፄ ዮሐንስ ጦር ጋር ተዋግተው የደረሰባቸው ሽንፈትና ትልቅ የሃፍረት ሸማ የተከናነቡበት የሚጠቀስ ነው፡፡ በጉራዕ ጦርነት ብቻ ግብፆች 14 ሺህ ወታደሮችን ያሰለፉ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ጦር ተደምስሶ በሞት፣በመቁሰልና በምርኮ ተጠናቋል፡፡ በሃያኛው ክፍለ ዘመን እንደዚህ ዓይነቱ ጊዜ ያለፈበት ወረራ የሚያዋጣ ባለመሆኑ ግብፆች ዘዴያቸውን ቀይረው ኢትዮጵያን በሚጐዳ የተለያዩ ድርጊቶችን ሲፈፅሙ ቆይተዋል፡፡ ግብፆች ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላት፤ አንድነቷ የተጠበቀ፤ ሉአላዊት ኢትዮጵያን ማየት ፈፅሞ አይፈልጉም፡፡ ስለዚህም በየጊዜው ኢትዮጵያን ለማዳከም የውስጥ ቅራኔዎችን በማባባስና በጐረቤት ሀገሮች በኩል ሰላሟን ለሚነሳ የጠብ አጫሪነት ሥራ ወታደራዊ ድጋፍ ሲሰጡ ቆይተዋል አሁንም ከዚህ ድርጊታቸው ይቆጠቡ ይሆናል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡
ከሚጠቀሱት ዋና ዋናዎቹ እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ1953 ዓ.ም በኤርትራ ፌደሬሽኑ መፍረስ ምክንያት ያኮረፉትን እነ እድሪስ አዋቴን ካይሮ ላይ በመሰብሰብ የኤርትራ ነፃነት ግምባር ወይም ጀብሃ እንዲመሰረት በማድረግ ወታደራዊ ስልጠናና የትጥቅ ዕርዳታ በመስጠት በኢትዮጵያ ረጅም ጊዜ ለወሰደው የወንድማማቾች ጦርነት ቡራኬውን የሰጠች ግብፅ ናት፡፡ በዚህም የብዙ ዜጐቻችን ሕይወት ከመጥፋት አልፎ ብዙ ሐብት የፈሰሰባቸውን የመሠረት ልማት አውታሮችን በማውደም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ያሽመደመደ ጦርነት እንደነበር የቅርብ ጊዜ መጥፎ ትዝታችን ነው፡፡ ፍፃሜውም የሀገሪቱን ዕጣ ፋንታ ሁለት እንድትከፈል ከማድረጉም በላይ ወደብ አልባም እንድትሆን አድርጓል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ግብፅ መንግስት አልባ በነበረችው የሶማሊያ ጉዳይ እጇን በማስገባት ድብቅ ፍላጐቷን ለማስፈፀም ሰርገው በገቡ ዓለምአቀፍ ፅንፈኛና አክራሪ ኃይሎች ድጋፍ በመስጠት የኢትዮጵያን ሰላም ለመንሳት ያላቋረጠ ጥረት አድርጋለች፡፡ ከእነዚህ ቡድኖች ውስጥ ከቅርብ ዓመታት በፊት በሶማሊያ ስልጣን ለመያዝ በቅቶ የነበረው የእስላሚክ ፍ/ቤቶች ሕብረት የተባለ አክራሪ ቡድንን ከጀርባ ሆነው አድራጊ ፈጣሪ የነበሩት ግብፆች መሆናቸው የተደበቀ አይደለም፡፡
በተለያዩ ጊዜ የነበሩ የግብፅ መንግስታት ከዘውዳዊው ፈርኦኖች እስከ ግራ ዘመም ፖለቲካ አራማጅ የነበሩ መሪዎቿ በሙሉ አንድም ቀን ኢትዮጵያን በበጐ አይተዋት አያውቁም፡፡ የዚህ ምክንያት ደግሞ ግብፅ ሕልውናዬ ነው ለምትለው ለናይል ወንዝ ውኃ 86% መነሻው ኢትዮጵያ በመሆኗ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን እውነታ ስናይ እስካሁን ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ባገኘችው የውኃ ፀጋ ጠላትን እንጂ ውለታና ሐብትን እንዳላፈራችበት የሚያሳይ ይሆናል፡፡ የአባይ ሸለቆ ጂኦ ፖለቲካ በኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የነፃነት ታሪክ ውስጥ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለብሔራዊ ጥቅሟና አንድነቷ ፈታኝ ሁኔታዎችን ሲያስከትልና ዕድገቷንም ሲጐትት እንደኖረ የሚታወቅ ነው፡፡  
ይሄንን ሁሉ ወደኋላ ተመልሼ ለመፃፍ የተገደድኩት ታሪክ ለመዘገብ ፈልጌ ሳይሆን ነገር ግን እስከዛሬ በአባይ ያተረፍነው ነገር ቢኖር የመሬት መራቆትን፣ ድሕነትንና ጦርነትን መሆኑ ለማንሳት ፈልጌ ነው፡፡
በአንፃሩ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በናይል ወንዝ ላይ ካሏቸው ሰፋፊ ዘመናዊ እርሻዎች በተጨማሪ የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦችም ያሏቸው ሲሆን ለከተሞቻቸው የመጠጥ ውኃ አቅርቦቱንም የሚያገኙት ከዚሁ ወንዝ ነው፡፡ በተጨማሪም ለትራንስፖርት አገልግሎት በሰፊው እየተጠቀሙበት ይገኛል፡፡ በዚህ ምክንያት ከወንዙ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታዎችን እያገኙ እንደሆነ የተረጋገጠ ነው፡፡ በናይል ወንዝ ላይ ሱዳንና ግብፅ ካሏቸው ግድቦች ውስጥ የሰንአርና የታላቁ አስዋን ግድብ የሚጠቀሱት ይሆናሉ፡፡ በሱዳን ያለው የሰነአር ግድብ የተገነባው በቀጥታ በጥቁር አባይ ወንዝ ላይ ሲሆን በዚህም በገዚራ አካባቢ ሰፊ የመስኖ እርሻ ማልማት ያስቻለ ነው፡፡ የግብፅን ስናይ ደግሞ ከሱዳን አዋሳኝ ካላቸው ዋዲ ሃልፋ እስከ ሚዲትራኒያን ባህር ጫፍ ያሉት ሮዜታና ዳሜታ ድረስ ባለው ብዙ ሺህ ኪ/ሜትር ተፋሰሱን ተከትሎ ከአመት እስከ አመት ውኃ ማቅረብ በሚችሉ ግድቦቻቸው አማካኝነት ሰፊ የሆነ የመስኖ እርሻ ማልማት የቻለች ሲሆን ይህም በአንድ ወቅት በጥጥ ምርት ከዓለም ቀዳሚውን ደረጃ እንድትይዝ አስችሏታል፡፡ የስንዴና የሸንኮራ አገዳ ተክልም በጣም ሰፊ የሚባሉ ቦታዎችን ከሚሸፍኑት የምርት አይነቶች የሚጠቀሱት ይሆናል፡፡ ከዚህ ውጪም ከኢትዮጵያ ተሸርሽሮ የሚሄደውን ለም አፈር በርሐማ አካባቢዎችን ከማዋላቸውም ከሚሞላቸው በላይ Egyptian Soil ተብሎ ወደ ውጪ ሀገራት በመላክ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ በመሆን በዱባይና በብዙ የአረብ ሀገራት የምናየው ነው፡፡ በአጠቃላይ 95% የሚሆነው የግብፅ ሕዝብ የሚኖረው ውኃውን ተከትሎ የሀገሪቱን የቆዳ ስፋት 5% በሚሸፍነው በናይል ሸለቆ ውስጥ ነው፡፡
ስለዚህም ከላይ በዝርዝር በተገለፀው መሠረት የአባይ ወንዝ እስካሁን ባለው ሁኔታ ለኢትዮጵያ የመሬት መራቆት፣ ድሕነትና ጦርነትን ያተረፈላት ሲሆን ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ደግሞ ዕድገትን፣ ብልፅግና፣ ፀጋንና ብርሃንን አጐናፅፏቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በአባይ ጉዳይ በቁጭት አይምሮውን እንዲያሰላስል ሲያደርግ የቆየ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ለዚህም ነው የዚህ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግምባታ ኘሮጀክት እያንዳንዱ ዜጋ የእኔ ጉዳይ ነው ይመለከተኛል በሚል እንደ አንድ ሆኖ የተነሳው፡፡ በዚህም መንፈስ ነው የዚህን የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኘሮጀክት ለማየት በቦታው ላይ የተገኘነው፡፡ የጉብኝቱም ውጤት በግድቡ ኘሮጀክት መጀመር የፈጠረብንን መነሳሳት የበለጠ ጠንካራ እንዲሆን ያደረገና ኘሮጀክቱም በታሰበው ጊዜ እንዲጠናቀቅ የበኩላችንን አስተዋፅኦ እንድናደርግ በድጋሜ ቃል የገባንበት እንዲሆን አድርጓል፡፡
በጉብኝታችን መጀመሪያ ላይ የኘሮጀክቱ ሥ/አስኪያጅ ኢ/ር ስመኘው በቀለ በአባይ ወንዝ የነበረንን ያለፈ ታሪካችንን ጭምር በማጣቀስ እንዲሁም የግድቡን ኘሮጀክት አጀማመርና አሁን የደረሰበትን ደረጃ እንዲሁም ፍፃሜው ለሀገሪቱ የሚያስገኘውን ጥቅም በማስመልከት ያደረጉት ገለፃ የብዙዎቻችን ስሜት መግዛት የቻለ ነበር፡፡ ይህ ኘሮጀክት ሞቃታማ የአየር ንብረት ባለበትና በተራራማ የመልክዓ ምድር በተላበሰ የአባይ ሸለቆ ውስጥ የሚሰራ ሲሆን በተለይ ዋናው ግድብ ያረፈበት ሥፍራ እስከዛሬ ምድር በተፈጠረች ጀምሮ የሰው ልጅ በቦታው ላይ ኖሮ እንደማያውቅ መገመት የሚቻል ነው፡፡ የአካባቢውን ግራ ቀኝ በጥሞና ስቃኝና ቀድሞ የነበረውን ሁኔታ ሳጤን ልጄን እስኪ ተረት አውራልኝ ብዬ ስጠይቅ የታሪኩን ጭብጥ አስፈሪ ገፅታ ለመስጠት ሲፈልግ “In the Middle of No Where” ብሎ የሚጀምረውን እንዳስታውስ አድርጐኛል፡፡ ይህ ሁኔታ ግን አሁን ነበር ሆኗል፡፡ 8500 ሠራተኞች በአንድ የሚሯሯጡበት በብዙ መቶ የማቆጠሩ ከባድ መኪናዎችና ማሽነሪዎች የሚተራመሱበትና ድምፃቸውም የሚያጓራበት እንዲሁም አልፎ አልፎ ተራራውን የሚንዱ አስፈሪ የፈንጂ ድምፅ የሚሰማበት አካባቢ ሆኗል፡፡
ሀገራችንም በትልቅ ተስፋ የምትጠብቀውና በየዕለቱ የኘሮጀክቱ ስም በተደጋጋሚ በሚዲያዎች እንዲነሳ የሆነና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጐች ልብ ውስጥ የተቀረፀና ለሀገሪቱም ትንሳኤ ይሆናል ተብሎ የተገመተ ኘሮጀክት የሚገነባበት አካባቢ ሆኗል፡፡ በዚህ ኘሮጀክት ርዝመቱ 246 ኪ.ሜ የሆነና 65 ቢሊዮን ሜ.ኪብ ውኃ መያዝ የሚችል ሰው ሰራሽ ሐይቅ በመፍጠር በ16 ተርባይኖች 6000 ሜጋ ዋት የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል ሲሆን ለቱሪዝም ኢንዱስትሪና ለአሳ ሀብት ልማት ትልቅ አስተዋፅኦ በማድረግ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ኘሮጀክቱም ሲጠናቀቅ እስካሁን ያለውን አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት /GDP/ ትርጉም ባለው መልኩ ሊያሳድግ ከመቻሉም በላይ በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የኃይል እጥረት በመቅረፍ በዜጐች ሕይወት ላይ በተለይም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ አዲስ የአኗኗር ባህል እንዲፈጠር የሚያስችልና የውጪ ኢንቨስትመንትንም በመሳብ በኩልም ሀገራችንን ተመራጭ እንድትሆን የሚያደርግ ነው፡፡ የኤሌትሪክ ኃይልም በመሸጥም ለሀገሪቱ ተጨማሪ የውጪ ምንዛሬ የሚያስገኝ መሆኑንም ስናይ ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ መሆኑን ያረጋግጥልናል፡፡
ከዚህ ኘሮጀክት በተጓዳኝነት ባለፉት 2 ዓመታት እየተከናወነ ያለው የተፋሰስ ልማት እንቅቃሴ የተራቆተውን አካባቢ በመልሶ ማልማት አረንጓዴ በማልበስ ሙሉ ለሙሉ የአፈር መሸርሸርን ከመከላከል አልፎ የወንዙን የውኃ መጠን እንዲጨምር የሚያደርግና ለግድቡ ዕድሜም ማጠር ምክንያት ሊሆን የሚችለውን ደለል የሚያስቀር ይሆናል፡፡
የኘሮጀክቱ የግምባታ ሥራ በአሁኑ ሰዓት አብዛኛው የግድቡ የመሠረት ሥራ ተጠናቆ የዋናው ግድብ የኮንክሪት ሙሊት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ እስካሁን ከተከናወኑት ዋና ዋና ሥራዎች ውስጥ ወደ ኘሮጀክቱ ሳይት እንዳስብ መግባት የሚያስችል የመንገድ ሥራ፣ በሥራው ላይ ለተሰማሩ 8500 ሠራተኞች የተሟላ መጠለያ ማዘጋጀት፤ ዋናውን የግድብ ግንባታ ለማከናወን የወንዙን አቅጣጫ ማስቀየርና፤ የኮንክሪት ሥራዎችን የተቀላጠፈ እንዲሆን የሚያደርጉልን የጠጠርና የኮንክሪት ባቺንግ ኘላንቶችን ተክሎ በበቂ ሁኔታ ምርቱን ማዘጋጀቱና ለኤሌትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚረዱ የመካኒካል ቁሶችን ወደ ሥራው ቦታ እንዲዳረሱ ማድረጉ የሚጠቀሱት ይሆናሉ፡፡ ከዚህ በኋላ በዋናነት የሚሠራውን የግድቡን ሥራ ለማጠናቀቅ እስካሁን የወሰደውን ጊዜ ያህል ሊወስድ እንደማይችል እንደባለሙያ መገመት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም በዋናነት ለኘሮጀክቱ መጣደፍ ወሳኝ የሆነው የኮንክሪት ሙሊት ሥራ በቀን 12,500 ሜ.ኩብ የማምረት አቅም ባለው ባቺንግ ኘላንት እየተከናወነ መሆኑ ግምታችን ትክክለኛ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
የዚህ ኘሮጀክት ዕውን መሆን ርቀን ሳንሄድ በቅርብ ያሉንን የተፈጥሮ ሀብታችንን እንድንፈትሽና ያሉትን አማራጮች ሁሉ በማየት የማልማት ደረጃ ላይ ብንደርስ በቀላሉ ከድሕነት መውጣት እንደምንችል ያረጋገጠልን ነው፡፡ ባሉን በርካታ የውኃ ተፋሰሶች ላይ ያተኮረ ኘሮጀክት ተግባራዊ ቢሆን ከሀገራችን እድገት አኳያ የሚኖረው ፋይዳ ቀላል  የሚባል አይሆንም፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኘሮጀክት የውኃውን ፍሰት ከአመት እስከ አመት የተመጣጠነ እንዲሆን የሚያስችል ከመሆኑም በላይ በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ የማያስከትልና እንዲያውም ጉልህ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ የኘሮጀክቱም ጥንትና ትግበራ ፍሕሃዊነትንና የጋራ ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ የዚህ ኘሮጀክት መሰራት እስከዛሬ በነበረው የወንዝ ፍሰት ምክንያት በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ሲያደርስ የቆየውን የጐርፍ መጥለቅለቅ ሙሉ ለሙሉ የሚያስቀር ይሆናል፡፡
ይህ ኘሮጀክት ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት እንዲህ ዓይነቱ ጠቀሜታ ያለው ከሆነ ለምንድን ነው ግብፆች ኘሮጀክቱን በአሉታዊ መልኩ የማያዩት? የሚለውን ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል፡፡ ግብፅ አሁንም ኢትዮጵያን የምታይበት መነፅር አልተቀየረም አሁንም ባረጀና ባፈጀ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ላይ እንዳለች ማወቅ ይቻላል፡፡ “ታሪካዊ የውኃ ሀብት ተጠቃሚነት መብት” በሚል በቅኝ ግዛት ዘመንና የታችኛዎቹ ተፋሰስ ሀገራት በተናጠል ያወጡትን ሕግ እንደመከላከያ ያቀርባሉ፡፡ ኢትዮጵያ የማንም መብትና ጥቅም እስካልነካች  የራሷንም መብትና ጥቅም አሳልፋ መስጠት አይኖርባትም፡፡ ስለዚህ ወንዞቿ ላይ ለምታከናወነው ልማት የሌሎች ሀገራትን በጐ ፈቃደኝነት መጠበቅ አይኖርባትም፡፡ ስለዚህም እስካሁን እንደተጓዘችበት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ባተኮረ መርኸ ወደፊትም በሌሎች ኘሮጀክቶች ላይ ልትቀጥል ይገባል የሚል አመለካከት አለኝ፡፡
ይህ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኘሮጀክት ጉብኝታችን የመጀመሪያ እንጁ የመጨረሻ እንደማይሆን ሁላችንም በጉብኝቱ ማጠቃለያ ላይ ቃል የገባን ሲሆን የጉብኝተችን መሪ መፈክር የነበረው “ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሀገራችን የኮንስትራክሽን ዕድገት ነፀብራቅ ነው” በሚል የተጀመረውን “የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኘሮጀክት በማጠናቀቅ የኢኮኖሚ ዕድገታችንም ነፀብራቅ እንዲሆን ሁላችንም የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል” የሚል መሪ መፈክር በአይምሮአችን በማስቀመጥ ለኘሮጀክቱ ስኬታማነት እንደትላንቱ ሁሉ ወደፊትም እስከ ኘሮጀክቱ ፍፃሜ ድረስ ተገቢውን ጥረት ማድረጉ ከሁሉም ዜጐች የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው፡፡